አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ የሰላም፣ የይቅርታና የእርቅ ተምሳሌት መሆኑን በተግባር ስላሳያችሁ ምስጋናዬ የላቀ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል
“ኢሬቻ የሰላም፣ የይቅርታና የእርቅ ተምሳሌት መሆኑን በተግባር ስላሳያችሁ ምስጋናዬ የላቀ ነው!
የኦሮሞ ህዝብ ሰላም ወዳድ፣ ለወንድማማችነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥና ባህሎቹም ሰላምን የሚያጎለብቱ ናቸው። በሆራ ፊንፊኔና በሆራ አርሰዴ የተከበረዉ የኢሬቻ በዓልም እሴቶቹንና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁ ይህንኑ እውነታ ያረጋገጠ ነው። የበዓሉ ባለቤት የሆነውና ሥርዓቱን ከነ እሴቶቹ ጠብቆ ያቆየው የኦሮሞ ህዝብም በባህላዊ አልባሳት አጊጠው ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት ከመሆን አልፎ የቱባ ባህል ባለቤት፣ ሰላም ወዳድ እና አቃፊ መሆኑን አረጋግጧል።
ኢሬቻ እንደ እሴቶቹ ሁሉ ሰላምና እርቅ የሚሰበክበት፣ አንድነትና ወንድማማችነትን የሚጠናከርበት መሆኑን በሆራ አርሰዴ በተከበረው ኢሬቻም ዳግም በማረጋገጥ ውድቀታችን ለሚጠብቁ አካላት ሀፍረትን፤ ደስታችንን ከኛ ጋር ለተካፈሉ ክብርን አጎናፅፏል።
በመሆኑም፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ ቄሮና ቀሬዎች፣ በየደረጃው ያላችሁ የመንግስት መዋቅርና የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌዴራልና የክልላችን የፀጥታ መዋቅር እንዲሁም መላዉ የኦሮሞ ህዝብ ከዋዜማው ጀምራችሁ እስከ መጨረሻው ድረስ በዓሉ ሥርዓቱን ጠብቆና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከበር እንዲሁም የበዓሉ ታዳሚዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ወደቤታቸው እንዲመለሱ ስላደረጋችሁ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው።
የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም አለም አቀፍ እንግዶች የተከበረውን በዓላችንን ከኛ ጋር በማክበር ለኛ ያላችሁን ክብር፣ ፍቅርና ወንድማማችነት ስላሳያችሁት አመሰግናችኋለሁ።
የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች የኢሬቻን በዓል ለማክበር ወደ ከተማቹ የመጡትን እንግዶች በእንግዳ ተቀባይና ወንድማማችነት በተሞላ ስሜት ተቀብላችሁ በማስተናገዳችሁ ምስጋና ይገባችኋል።
ለተከበረው ሙያችሁ ታምናችሁ በተለያየ ቋንቋ ኢሬቻ የሰላም፣ የይቅርታና የእርቅ ተምሳሌት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት ዓርማ መሆኑን ለአለም ህዝብ አይንና ጆሮ ያደረሳችሁ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም 2016 ዓ.ም የእርቅና የይቅርታ፣ አንድነታችን የሚፀናበት፣ ወንድማማችነታችን ይበልጥ የሚያብብበት እንዲሆንልን እየተመኘው ዘመኑ የኦሮሞ ህዝብ እርስ በርሱን ተደማምጠዉ የሀሳብ ለዩነቶቹን በምክክርና በዉይይት በመፍታትና ሰላሙን በማስፈን ልማቱን የሚያፋጥንበት እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ!
አመሰግናለሁ!
ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
መስከረም 27/2016 ዓ.ም
ፊንፊኔ