Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሠራዊቱ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅበታል- ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ከዕዙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዕዙ የግዳጅ አፈፃፀም ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በክብር እንድትደርስ ብዙዎች መስዋዕትነት የከፈሉላት ታላቅ ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

“ሀገር ለማፍረስ ጥቅማቸውን በሠራዊቱ ላይ ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች ቢኖሩም እኛ የሀገራችን የመጨረሻ ምሽግ ሆነን ተልዕኳችንን እየፈፀምን እንገኛለን” ብለዋል።

አያት ቅድመ አያቶቻችን ኢትዮጵያን ከነ ክብሯ እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም የሚጠበቅብንን መስዋዕትነት በመክፈል ለመጪው ትውልድ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀና ነፃነቷ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና አንድነቷን ለመናድ የውጪም ሆኑ የውስጥ ጠላቶቻችን ብዙ ጥረት ቢያደርጉም፤ ኢትዮጵያ ግን በጀግኖች ልጆቿ ቆራጥ ተጋድሎ ከመበተን መዳኗን አንስተዋል፡፡

“አሁን በቀጠናችን ያሉ ፅንፈኛና የዘራፊዎች ቡድን ስብስብ ዓላማም የታሪካዊ ጠላቶቻቸንን አጀንዳ ማስፈፀም ነው” ብለዋል፡፡

ተልዕኳችንን በላቀ ብቃት በመፈፀም የህዝቦችን ደህንነት ማረጋገጥና የሀገራችንን የልማት ጉዞ ለማሳካትም አስተማማኝ የሠላም ዘብ መሆናችንን አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜ/ጄ ሙሉዓለም አድማሱ በበኩላቸው÷ ሰራዊቱ በስርዓት የተገነባ፣ የትም ቦታ ሄዶ ግዳጅና ተልዕኮን መወጣት የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ይህ ያልተመቻቸው ፅንፈኞች ሠራዊቱን ለማፍረስ ብዙ ሞክረዋል ፤ነገር ግን ሙከራው አልተሳካላቸውም ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version