አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአይሱዙ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ፣ሽያጭና ድህረ ሽያጭ ማዕከል በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ÷የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲመረቱ የሎጅስቲክስ ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚያስፈል ገልጸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የሀገር ውስጥ ምርቶች ተመራጭ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የጃፓን ስሪት የአይሱዙ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ፣ የሽያጭና ድህረ ሽያጭ ማዕከል መከፈቱ ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠርና ሀገራዊ ኢኮኖሚን ከመደገፍ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ማዕከሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የካኪ ሞተርስ የግል ኩባንያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ገ/ሚካኤል ግርማይ ናቸው፡፡
ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ሲሰራ በዓመት 2 ሺህ 500 የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንደሚያመርት መገለጹንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በመርሐ ግብሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮን ጨምሮ ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል፡፡