አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ ተጥሎ በነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል መንገሻ ፈንታው( ዶ/ር) ÷በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በኮማንድ ፖስት የሰዓት እላፊ ተጥሎ እንደነበር አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ በክልሉ በተደረገ የሰላም ማስከበር ስራ አንጻራዊ ሰላም መገኘቱን ተከትሎም ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በባህር ዳር፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ሰዓት እላፊው 2 ሰዓት ከነበረበት ወደ 3 ሰዓት ከፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የሌሎቹ አከባቢዎችም በኮማንድ ፖስቱ እየተገመገመ የሚታይ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በባጃጆች ላይ የተጣለው ሰዓት እላፊ በጎንደር ከተማ እስከ 2 ሰዓት ከፍ ሲደረግ ÷ በሌሎቹ አካባቢዎች ግን እስከ 1 ሰዓት ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ግምገማ ያደረገ ሲሆን÷በዚህም ሕብረተሰቡ ሰላም ወዳድ በመሆኑ ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመስራት አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ ሆኗል ተብሏል።
አሁን ላይ ከአንድ አንድ ራቅ ካሉ ወረዳዎች ውጪ ሕብረተሰቡ መደበኛ እንቅስቃሴውን ማድረግ መጀመሩም ተጠቅሷል።
በታሪኩ ለገሰ