አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠራዊቱ አመራሮች እና አባላት የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁነታቸውንና የማድረግ ዐቅማቸውን በማሣደግ የዓላማ ጽናታቸው ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳሰቡ፡፡
“በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚጸና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሐሳብ 116ኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “የውስጥ ግጭቶችን በመመከት ተልዕኮ አኩሪ ተግባር እየፈጸማችሁ ለምትገኙ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ከፍተኛ ክብር ይገባችኋል” ብለዋል፡፡
ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር የተረከብናትን ሀገር እንደታፈረችና እንደተከበረች ለማስቀጠል ወታደራዊ ቁመናችንን አሳድገንና አዘምነን ተልዕኳችንን በላቀ ብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ለሕዝባችን እናረጋግጣለንም ነው ያሉት በንግግራቸው፡፡
“የሠራዊታችንን ዝግጁነት በማዳበር የማድረግ ዐቅማችንን በማሣደግ የውጭም ሆነ የውስጥ የጸጥታ ሥጋትን እየመከትን ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የምድር፣ የዓየር፣ የባሕር እና የሳይበር ኃይላችንንም ዘመኑን እና ኢትዮጵያን በሚመጥን ሁኔታ በመገንባት አስተማማኝ ደረጃ ላይ አድርሰናል ነው ያሉት፡፡
ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ረገድም ሠራዊቱ በትጋት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የታጠቁ ኃይሎችን እና ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት እየተሠራ ያለው በሱዳን የተከሰተው ችግር በኢትዮጵያም እንዳይከሰት በማሰብ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የሠራዊቱ ጥንካሬ በየዘርፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጥቀስም፥ ሠራዊቱ ያልተቋረጡ ስምሪቶችን እያከናወነ ያለው ለሀገር ዘላቂ ሠላም መሆኑን አንስተዋል።
የሠራዊቱ አመራሮች እና አባላት እስከዛሬ እንዳደረጋችሁት ሁሉ ወደፊትም የተጣለባችሁን የሀገር እና ሕዝብ አደራ ለመወጣት ዝግጁነታችሁን እና የማድረግ ዐቅማችሁን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የዓላማ ጽናታችሁና ጀግንነታችሁ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ ተልዕኳችሁን በአስተማማኝ ሁኔታ እየተወጣችሁ ለመቀጠል በዚህ ታሪካዊ ቀን ቃላችሁን እንድታድሱና ተግባር ላይ እንድታውሉ አሳስባለሁ ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!