Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ እና አየርላንድ የ8 ነጥብ 4 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር እና የአየርላንድ መንግሥት የ8 ሚሊየን 400 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የአየርላንድ የዓለም አቀፍ ልማትና ዳያስፖራ ሚኒስትር ዴዔታ ሾን ፍሌሚንግ ናቸው፡፡

በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ ወቅት እንደተገለጸው ስምምነቱ ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን÷ የመጀመሪያው 5 ሚሊየን ዩሮው ለሴፍቲ ኔት ፕሮግራም እንዲሁም 3 ሚሊየን ዩሮው በጤና ላይ ያተኮሩ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለመደገፍ የሚውል ነው፡፡

400 ሺህ ዩሮው ደግሞ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ድጋፍ እንደሚውል መገለጹን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ አሕመድ ሽዴ ከፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር÷ አየር ላንድ ለኢትዮጵያን የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እያደረገችው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ሦስቱም ስምምነቶች በመንግሥት በኩል ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር  ተጣጥመው እንደሚተገበሩም አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታ ሾን ፍሌሚንግ በበኩላቸው÷ እነዚህ ሀገራዊ መርሐ- ግብሮች የማህበራዊ ጥበቃ እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው በተለይም ሴቶች እና ሕጻናትን ለመድረስ እንዲተገበሩ ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version