ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን÷ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ህይወት ሳይጠፋና የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የተቀናጀ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።
በክልሎቹ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በሚመለከት አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚሹትን በመለየት ዝርዝር እቅድ አዘጋጅቶ ማስፈጸም ይገባልም ብለዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ጉዳይ የሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ለዚህም የሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በዘላቂነት በራስ አቅም መቋቋምና ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሀገሪቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት እየተተገበሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር አደጋዎችን መሸከም የሚችል ሀገራዊ አቅም በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ለስኬቱ የሁሉም ርብርብ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።
በየዘመኑ በርካታ ሰው ሰራሸና የተፈጥሮ አደጋዎች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው ህዝቡ አደጋዎችን በፅናት በመቋቋም መሻገሩን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ይህን ጠንካራ ሀገርና ህዝብ የሚመራው አመራር ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ከተረጂነት ለመላቀቅ በጋራ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ክልሎች በየአካባቢያቸው ችግሮች እንዳይከሰቱ ሲከሰቱም በራሳቸው አቅም ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) “ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ገመናና ሉዓላዊነት፣ ፈተናዎችና የመውጫ መንገዶች” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመወያያ ፅሁፍ አቅርበዋል።
በፅሁፋቸውም ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት አደጋ ባጋጠማት ጊዜ ሁሉ በተረጂነት መቆየቷን ጠቅሰው ይህም ሉዓላዊነታቸው ምልዑ እንዳይሆን አድርጓል ነው ያሉት።
በመሆኑም ክብራችንን ለማስጠበቅና ከተረጂነት ለመላቀቅ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎታችንን በራስ አቅም መሸፈን እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

