Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የገንዘብ ሚኒስቴር እና ገቢዎች ሚኒስቴር  የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስቴር እና በገቢዎች ሚኒስቴር መካከል የታክስ ፖሊሲና አስተዳደር ጉዳዮችን በቅንጅት ለማከናወን የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የፕሮቶኮል ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ናቸው።

አቶ አሕመድ ሺዴ እንደገለጹት÷ ስምምነቱ ያስፈለገው የታክስ ፖሊሲን የሚያመነጨውና አፈፃፀሙን የሚከታተለው የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የታክስ አስተዳደሩን የሚመራው የገቢዎች ሚኒስቴር ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡

በተጨማሪም ሥራቸውን በቅንጅት እንዲመሩ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ስምምነቱ ተፈርሟል ማለታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው÷ የታክስ ፖሊሲ እና የታክስ አስተዳደር ጉዳዮች ተጣጥመው እና በተቀናጀ አኳኋን እንዲመሩ ማድረግ መንግሥት በታክስ አማካኝነት የሚያስፈፅማቸውን የኢኮኖሚ አጀንዳዎች ከግብ ለማድረስ ስምምነቱ አስፈልጓል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ለልማት ሥራዎች ማስፈፀሚያ የሚያስፈልገውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ ወሳኝ በመሆኑ የፕሮቶኮል ስምምነቱ መፈረሙን ነው የገለጹት፡፡

Exit mobile version