Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ኮማንድ ፖስቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማሸጋገር የክልልና የዞን መስተዳድር አካላት ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌ/ጄ ብርሀኑ በቀለ ተናገሩ።

ኮማንድ ፖስቱ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ ከክልልና ከቀጣናው የዞን መስተዳድር አካላት እንዲሁም ከሚመለከታቸው የፀጥታና የደኅንነት መዋቅር ኃላፊዎች ጋር በአሁናዊ የግዳጅ አፈፃፀም እንዲሁም በቀጣይ የግዳጅ አፈፃፀም የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይቷል።

ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ በወቅቱ÷ ፅንፈኛና የዘራፊ ቡድኑ ስብስብ እየተወሰደበት ባለው እርምጃ እየተበታተነ ይገኛል፤ እየፈፀመ ባለው አሳፋሪ ድርጊትም ከሕዝቡ ተነጥሏል ብለዋል፡፡

በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ እንደሌለውም በሚፈፅማቸው የዝርፊያና የውንብድና ተግባሩ እየተረጋገጠ ነው ማለታቸውንም ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አሁን እየታየ ያለውን አንፃራዊ ሠላም ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስና ሕዝቡ ወደ ቀደመ ማህበራዊ ህይወቱ እንዲመለስ በቡድኑ ላይ የተጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሕብረተሰቡ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን ተጨባጭ እውነታውን ማስገንዘብና ህዝብን ያሳተፈ ቅንጅታዊ የፀጥታ ስራ ማከናወንና ህዝባዊ ውይይቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠልና ሰላም ፈላጊውን ሕዝብ በቅንነት ማገልገል ከእያንዳንዱ አመራር እንደሚጠበቅ በመገንዘብ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ወደ ስራ መግባት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

Exit mobile version