Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሀገር ውስጥ ገቢና ወጪ ላይ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት ገቢና ወጪን በተመለከተ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠበቁ አሃዞች ማመላከታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡

የመንግሥት ገቢና ወጪን በተመለከተ ምንም እንኳ አሁንም ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም በአሃዝ ደረጃ ሲታይ የገቢ መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

በ2011 በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢ 235 ቢሊየን እንደነበር አስታውሰው÷ ባለፈው ዓመት 407 ቢሊየን መድረሱን አስረድተዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመትም የሀገር ውስጥ ገቢን 520 ቢሊየን ለማድረስ መታቀዱን ነው ያመላከቱት፡፡

በተጠናቀቀው ሩብ ዓመት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መግባቱን ገልጸው፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 12 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ወጪን በተመለከተም ባለፉት ሦስት ወራት 141 ቢሊየን ወጪ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ማደጉን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በአጠቃላይ ገቢና ወጭ ላይ ያለው ሁኔታ ጥሩ ቢሆንም ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ100 በላይ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመው÷ ቁጥራቸው እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

31 ገደማ የንግድ ባንኮች፣ 48 ገደማ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ 6 የክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች፣ 6 የካፒታል ዕቃዎች ገቢ ላይ የሚሠሩ ኩባንያዎች 7 የሞባይል ዋሌት አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማት መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክም ከጥቂት የፋይናንስ ተቋማት በርካታ የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር ኃላፊነቱ መስፋቱን ጠቅሰው÷ ይህን ኃላፊነት ለማሳለጥም የሪፎርም ሥራዎች መከነወናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ የፋይናንስ ዘርፉ በየዓመቱ 20 በመቶ እያደገ መምጣቱንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version