አዲስ አበባ፣ ህዳር 7 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በቻይና ሻንጋይ ከተማ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እና ተቋማትን ጎብኝቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት የሁዋዌ ቴክኖሎጂ ማዕከልን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን፣ የሻንጋይ ከተማን እቅድና ዲዛይን እንዲሁም ደረቅ ቆሻሻን እንደገና ጥቅም ላይ የሚያውል ፕሮጀክትን ተመልክተዋል፡፡
የጉብኝት መርሐ ግብሩ በሻንጋይ ከተማ ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እቅድ፣ ትግበራ እና አፈጻጸም ልምድ ለመቅሰም ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ልዑካኑ ምልከታ ካደረጉባቸው ተቋማት አመራሮች ጋር የልምድ ልውውጥ ውይይት ማካሄዳቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በቻይና ሻንጋይ ከተማ የተመለከቷቸውን ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ መተግበር የሚያስችል ተሞክሮ ማግኘታቸውም ተጠቁሟል፡፡