Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የከተሞችን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ወደ ዲጂታል የማሸጋገር ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ከተሞችን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ዲጂታል የማሸጋገር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

እየተካሄደ በሚገኘው የመንግሥት የ2016 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ላይ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት÷ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን ለማዘመን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በሥድስት ከተሞች የአገልግሎት ደረጃዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከተሞቹ በቄራ አገልግሎት፣ በአረንጓዴ ልማትና የከተማ ውበት፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ወደ ዲጂታላይዜሽን ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአብነትም በቀብሪደሃር፣ ጅግጅጋ፣ ደብረ ብርሃን እና ቢሾፍቱ ከተሞችን ጠቅሰዋል።

በእነዚህ ከተሞች የሚገኘውን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ለማስፋት ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡

የከተሞች የመሬት አያያዝ ሥርዓትን ለማዘመን በካዳስተር ሥርዓት መመዝገብ መጀመሩን ጠቅሰው÷ ይህም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከከተሞች የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት 6 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡንም ገልጸዋል፡፡

የከተሞች የገቢ ዐቅም ማደጉ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር፣ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እና መሰረተ ልማቶችን በራስ ዐቅም ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version