Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት እንዲሆን ሐላፊነታችንን መወጣት አለብን – አቶ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማንኛውም ዜጋ ሰርቶ የሚለወጥበት፣ ፍጹም ሰላማዊና የዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሐላፊነት መወጣት አለብን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርእሰ መስተዳድሩ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ክልሉ የብዝሃ ባህል፣ እምነት ወግና ስርዓት ባለቤት ከመሆኑም ባሻገር አኩሪ ሰላምና እሴትም አለው ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች የታወቀ የግጭት አፈታት ስርዓት እንዳላቸው ጠቅሰው÷ የወንጀል ድርጊት የሚፈታበት ባህላዊ የፍርድ ስርዓት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ጸብን የሚያበርድ፣ የተጎዳን የሚክሱ፣ የተሰበረን የሚጠግኑ፣ ድንቅ አባቶችና እናቶች እንዲሁም ያባቶችን ትዕዛዝ የሚሰሙ ወጣቶች ያሉን ህዝቦች በመሆናችን ይህንን አኩሪ ባህል ተጠቅመን የክልሉን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።

በፈተናዎች ታጅቦ በዳበረ ውይይትና ሰላምን ቀዳሚ ባደረገ ወንድማማችነት በፍጹም መተሳሰብና መደጋገፍ የህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና ልማትን ማዕከል አድርጎ ለተደራጀው ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የምስረታ ስነ-ስርዓት እንኳን አደረሰን፤ አደረሳችሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ክልሉ የተመሰረተበት መንገድ በሀገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አይነተኛ ተምሳሌት ከመሆኑም በላይ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ እራሱ እንዲወስን ያደረገ ተግባር ነበር ብለዋል፡፡

የህዝቡ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ሂደቱ ባማረ መንገድ ተመርቶ ወደ ውጤት እንዲቀየር ላበቁት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዛሬ በይፋ ስራ መጀመሩን የምናበስርለት ክልል በተመቻቸ መንገድ የተመሰረተ አልነበረም ሲሉ አስታውሰዋል።

ለክልል መመስረት በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ ሃላፊዎችም ሲገጥሙ የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋምና በጽናት በመሻገር እንዲሁም በፍጹም መተሳሰብ የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማሰብ ክልሉ እንዲመሰረት ስላደረጋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ክልሉ ህዝቦች በተጠናከረ አንድነት ሰርተው የሚለወጡበትና የህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እንደሚሰራ አቶ ጥላሁን ከበደ ተናግረዋል።

በየሻምበል ምሕረት

Exit mobile version