አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 14 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በአንጎላ በተካሄደው 3ኛው የፓን አፍሪካ የሰላም ባህል ፎረም ላይ ተሳትፈዋል።
ፎረሙ በአፍሪካ ህብረት እና አንጎላ ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ጋር በጥምረት የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከአንጎላው ፕሬዚዳንት ጆኣኦ ሎሬንኮ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት የአንጎላ የነጻነት ትግል ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ ደረጃ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው በዚህ ወቅት አንስተዋል።
አያይዘውም ፎረሙ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከርን ጨምሮ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ያግዛል ብለዋል።
“የፓን አፍሪካ የሰላም ባህል ፎረም” አህጉራዊ የባህል ልውውጥን እና በትውልዶች መካከል ውይይቶችን በማበረታታት የሁከት እና ግጭት አፈታትን የማስተዋወቅ አላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል።