Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ አረንጓዴ ተኮር ኢንዱስትሪ እንደምትከተል ያላትን ተሞክሮ በተመድ የልማት ድርጅት ጉባዔ ላይ አካፍለዋል – ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ አረንጓዴ ተኮር ኢንዱስትሪ እንደምትከተል ያላትን ተሞክሮ በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ጉባዔ ላይ ማካፈላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡

ኃላፊዋ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦስትሪያ ቪየና ቆይታቸውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመድ የልማት ድርጅት የ20ኛው ጉባኤ ላይ በመገኘት የክብር እንግዳ በመሆን መልዕክት አስተላልፈዋል ብለዋል፡፡

በዋነኝነት ኢትዮጵያም በኢንዱስትሪ ዘርፍ እያደረገች ያለውን እንዲሁም አመርቂ ውጤት እንዳላት ሀገር በጉባኤው ልምዷን ማካፈሏንም ነው ያነሱት፡፡

ከጉባኤው በፊትም በተደረገው የከፍተኛ ልዑክ የእራት ሥነ-ስርዓት ላይ ለተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የኢትዮጵያን ተሞክሮ በምሳሌነት ሲያነሱ እንደነበረም ጠቅሰዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ያመጣቻቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንስተው ለተጋባዥ እንግዶች እንዳብራሩም ነው ኃላፊዋ የተናገሩት፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ የስንዴ ምርታማነቷ ሦስት እጥፍ መጨመሩን በተሞክሮ ማንሳታቸውም ተገልጿል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ካላት የምግብ ዋስትና ጋር ተያይዞ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ምስክርነት መስጠታቸውም ነው የተጠቀሰው፡፡

ከኢንዱስትሪያላይዜሽን ጋር ተያይዞ ባነሱት ሃሳብም ሀገራቱ በዘርፉ የሚያከናውኑትን ሥራ ፍትሃዊ እንዲያደርጉና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት እሴት ጨምሮ ኢኮኖሚን ለማሳደግና ዜጎች ገቢያቸው እንዲያድግ ማድረግን አስመልክተውም ሃሳባቸውን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባነሱት ሃሳብ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ከፖሊሲ አኳያ ለውጦች እያመጣች መሆኑን አስረድተዋልም ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር፣ የማክሮ ኢኮኖሚውን በማስተካከል ማሻሻያዎች ተፈጥረው ለኢንዱስትሪ ልማትና ለብዝሃ ዘርፍ ለምታደርገው ተሞክሮ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠሩላት መግለጻቸውም ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም በማምረቻው፣ በግብርና፣ በኢንፎርሚሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም ኢትዮጵያ እያመጣቻቸው ያለውን ለውጥ በተመለከተ ማካፈላቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ኢንዱስትሪ ተኮር የሆኑ ስራዎችን ለመስራት ከታዳሽ ኃይል ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሂደቱ አረንጓዴ ተኮር እንደሆነ በጉባኤው ላይ መመግለጻቸውንም አስረድተዋል።

ይህም ሌሎች ሀገራት የሄዱበትን መንገድ ላለመከተልና በአረንጓዴ ስትራቴጂ አቅም እንዳላትና ከሌሎቹ በመማር መስራትና ወደፊት መሄድ እንደምትችል ማንሳታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከኦስትሪያ መራሄ መንግስት ካርል ኔሄመርን ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከዚህ ባልተሰራባቸው የትብብር መስኮች ላይ አትኩረው መስራት እንደሚፈልጉም መናገራቸውንም ነው ኃላፊዋ የገለጹት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version