Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሃገራት አምባሳደሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ገለፃ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ እና አሜሪካ ሃገራት አምባሳደሮች ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገለጻ አድርጓል።
 
ገለጻው በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንደርጋቸው እና በአንጂነር ጌዲዮን አስፋው አማካኝነት ተሰጥቷል።
 
የገለጻው ዋና ዓላማ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ አምባሳደሮቹ ወቅታዊ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
 
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን እና በአሁኑ ሰዓት ሀይል ለማመንጨት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ በዚህ ወቅት ተገልጿል።
 
ከዚህ ባለፈም ግድቡ ለኢትዮጵያ፣ ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካ አህጉር የሚኖረውን ጠቀሜታ በተመለከተ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፥ የግድቡ ግንባታን በትብብር፣ በፍሃዊነት እና በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ኢትዮጵያ እየገነባች መሆኑም ተብራርቷል።
 
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ውይይቶች ማድረጋቸውን እና የነበሩ ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ ከዚህ ደረጃ መድረሳቸውን፥ በቀጣይ የሚኖሩ ልዩነቶችንም በተመሳሳይ በሶስቱ ሃገራት በሚደረጉ ውይይቶች ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗም ተገልጿል።
 
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታተ ድርጅት ዋና ፀሀፊ እና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በኩል የወጡ መግለጫዎችን ኢትዮጵያ እንደምታደንቅም በዚህ ወቅት ተነስቷል።
 
ከገላጻው በኋላ አምባሳደሮቹ በአሁኑ ሰዓት ሶስቱ ሃገራት ወደ ወይይት ስለመመለሳቸው፣ ቀጣይ በሚያደርጉት ውይይትና ድርድር የአፍሪካ ህብረት ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል ሀሳቦችን አንስተው ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
 
መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ነው።

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version