Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የስራ ጉብኝቶች የዲፕሎማሲ አቅምን ከፍ ያደረጉ ናቸው – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስራ ጉብኝቶች የዲፕሎማሲ አቅምን ከፍ ያደረጉ እንደሆኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ይፋዊ የስራ ጉብኝትን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተጠናከረ የመጣውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከጥቂት ሣምንታት በፊት የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፊያላ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር፥ በቼክ ሪፐብሊክ ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስድስት የልማት ቁልፍ ትብብር ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ከሀገራቱ የትብብር መስኮች መካከልም የቱሪዝምና ቅርስ ጥበቃ ምርምር ዘርፍ ይጠቀሳል፡፡

በዚህም መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሀገሪቱ ዋና ከተማ ፕራግ የሚገኘውን ብሔራዊ ሙዚየምን መጎብኘታቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ታሪኳን በመጠበቅና ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ልምድ ያላት መሆኑን መመልከታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ ጉብኝታቸውም ኢትዮጵያ ከዚህ ትልቅ ልምድ መውሰድ እንደምትችልና በተለይ ደግም ብሔራዊ አብሮነትና ሀገራዊ ትርክትን ለማጽናት እንዲሁም ትውልዱ ስለኢትዮጵያዊነት እንዲያውቅ ለማድረግ ዘመኑን የዋጀ ሙዚየም ሊኖር እንደሚገባ በስፋት አንስተዋልም ተብሏል፡፡

በዚህም ረገድ ቼክ ሪፐብሊክ ልምድ ያላት በመሆኑ የብሔራዊ ሙዚየም ግንባታ እንድታከናውን ጥሪ ማቅረባቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ምክክር፤ ሀገራቱ ታሪክን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱ ሲሆን፥ ይህ ግንኙነታቸውም በሌሎች ዘርፎች መደገም እንዳለበትም ነው በስፋት ያነሱት፡፡

በቼክ ቋንቋ የተጻፈው በኋላም የሐበሻ ጀብዱ በሚል የተተረጎመው መጽሃፍ ፀሀፊ ኢንጂነር አዶልፍ ፓርለሳክን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋጽዖ በተመለከተም አንስተዋል፤ ይሄም በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የሚገኝ ነውም ብለዋል፡፡

የፀሀፊ ኢንጂነር አዶልፍ ፓርለሳክ የትውልድ ከተማ የሆነችው ብሩኖም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጎብኝታለች፡፡

በዚያም በሚገኝ የግብርና መሳሪያዎችን የጎበኙ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች እንደሚያስፈልግ ተነስቷል፡፡

ይሄን ለማድረግም በቼክ ሪፐብሊክ ከሚገኙ በርካታ ተቋማት ውስጥ የተጎበኘው ኩባንያ በኢትዮጵያ ማምረት እንዲችል ጥሪ ቀርቦለታልም ነው የተባለው፡፡

በመንግስታቱ መካከል የተጀመረውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከፍ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተነሳው፡፡

በቅርቡ በፕራግ ሙዚየም በሚዘጋጀው ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ የተገለጸ ሲሆን፥ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማስተዋወቅ ሰፊ እድል ይሆናልም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቀጥታ ወደፕራግ ማድረግ እንዲችልና በወጪ ንግድ በቡና እና ሌሎች ምርቶች ያለውን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ የሚያስችል እድል መኖሩን በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወታደራዊ የአቅም ግንባታ ትብብር እንዳላቸው ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በተለይ በአየር ኃይል የስልጠናና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ላይ ሀገራቱ ጠንካራ ግንኙነት አላቸውም ብለዋል፡፡

በመሪዎች ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ሁለቱ ሀገራት የጋራ ኢኮኖሚ ትብብር ኮሚሽን ለማቋቋምም መስማማታቸውም ነው የተነሳው፡፡

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በነበራቸው የስራ ጉብኝቶች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች ማስከበር የሚችሉ እንደነበሩም ነው የተገለጸው፡፡

ይህም አዳዲስ የገበያና የፋይናስ አማራጮችን ለመፈለግ እንዲሁም የዲፕሎማሲ አቅምን ከፍ ለማድረግ ያስቻለ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በመሰረት አወቀ

Exit mobile version