Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በኮፕ28 የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ተሞክሮዎቿን ታካፍላለች – ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዱባይ በሚካሔደው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ተሞክሮዎቿን ለዓለም እንደምታካፍል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 28) በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በዱባይ መካሄድ ጀምሯል።

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ይሄንን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ÷ በስፍራው ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ኤግዚቢሽን በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገበችውን ስኬትና ሌሎች ተሞክሮዎችን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስራዋን በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ አውደ ርዕይ በማስተዋወቅ ላይ መሆኗንም ገልጸዋል።

በ1 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ትልቅ ኢግዚብሽን በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣች መሆኗን የምናሳይበት ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በጉባኤውም መሪዎች ንግግር በማድረግ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዙሪያ ድምጿን ታሰማለችም ነው ያሉት፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጉላት ዘላቂ የግብርና ልማት ተሳትፎዎች ላይ በማተኮር በስንዴ ልማት እምርታዊ ለውጥ መታየቱንም ጠቅሰዋል ሚኒስትሯ።

Exit mobile version