አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የብሪታኒያ ብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ በወንጀል መከላከል ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑክ በብሪታኒያ የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላም ከብሪታኒያ ብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይታቸውም ÷ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ መምከራቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
ፌደራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ዐቅሞችን በማሣደጉ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ በውይይታቸው ላይ አብራርተዋል፡፡
የብሪታኒያ ብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ለኦፕሬሽን ዴቪድ ሀከር÷ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በአዲስ አበባ የሚገኘውን የሬድ ፎክስ ማዕከል በቴክኖሎጂ እና በስልጠና እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ የፖሊስ አመራሮችና አባላት በብሪታኒያ የትምህርት ዕድል ለመስጠት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡