Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በልዩነት ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች መካከል አረንጓዴ አሻራ አንዱ ይሆናል – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣይ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በልዩነት ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው አረንጓዴ አሻራ ይሆናል ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ይዛ የቀረበችውን አውደ ርዕይ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በአውደ ርዕዩ ይዛ የቀረበችው የአካባቢ ጥበቃ ውጤት የአመራር ቁርጠኝነት የሚታይበት መድረክ ስለሆነ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት መሪዎች ጭምር ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያከናወነች ባለው ተግባርና ባስገኘችው ውጤት መደነቃቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም መሪዎቹ ባደረጓቸው ንግግሮች ሁሉ በዘርፉ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማሳያነት ሲጠቅሱ ተስተውሏልም ነው ያሉት።

በቀጣይ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በልዩነት ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው አረንጓዴ አሻራ ይሆናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሳየችው ተነሳሽነትና ያገኘችው ውጤት ለዓለም ከፍተኛ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ያሳያል ሲሉ አክለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ እና የስራ ዕድል የሚፈጠርበት ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ውጤት ተጨባጭ መሆኑን በቡና፣ በስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የተገኘው ውጤት ጥሩ ማሳያዎች ናቸውም ብለዋል ወይዘሮ ጫለቱ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የህብረተሰቡን አመለካከት ከመንቀል ወደ መትከል በማሸጋገር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ባህል ሆኖ በየዓመቱ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት እያደረገች ያለችው ድጋፍ እንደ አንድ ተሞክሮ የሚጠቀስ ነውም ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ፍራፍሬዎች በሀገር ውስጥ ገበያ እንደልብ እዲገኙ ከማስቻሉም በላይ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ዕድል የፈጠረ መሆኑንም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ግብርናውን ትራንስፎርም ማድረግና በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ መሳካት የሚችለው በአረንጓዴ አሻራ መሆኑን መረዳት ይገባልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው።

 

Exit mobile version