አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸዋል ኢድ በዓል በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ የብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡
ብልጽግና በትኩረት እና በልኅቀት እፈፅማቸዋለሁ ብሎ ከያዛቸው አምስት የልማት መስኮች የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አስታውቀዋል፡፡
አቶ አደም ባስተላለፉት መልዕክት “በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ መስኅቦች በይበልጥ እንዲያድጉና ለሀገራችን የብልፅግና ጉዞ ተጨማሪ ዐቅም መፍጠር እንዲችሉ ፓርቲያችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የሸዋል ኢድ በአል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከርና አድማሱን እንዲያሰፋ እንደሚያደርገውም ጠቅሰዋል።
ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ሐረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ አድርጓታል ብለዋል አቶ አደም፡፡
ኢትዮጵያንም በርካታ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን እንድትይዝ የሚያደርጋት በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ነው ያሉት።
በቀጣይም የበዓሉ አከባበር በይበልጥ ባማረ መልኩ እንዲቀጥል እና ድምቀቱ ዓለም አቀፍ እውቅናውን በሚመጥን መልኩ እንዲካሄድ፣ ከተማዋም በጎብኚዎች ዘንድ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እንደ ብልጽግና ፓርቲ ሰፊ ሥራዎችን መሥራታችንን እንደምንቀጥል አረጋግጣለሁ ብለዋል፡፡