አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊ ክልል ጅግጅጋ እየተከበረ ባለው 18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ለመታደም ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ ጅግጅጋ ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቷ ጅግጅጋ ሲደርሱ በሶማሊ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች አቀባበል እንዳደረጉላቸው ከክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዓሉን ለማክበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጂግጂጋ ከተማ ተገኝተዋል።
‘ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት’ በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው በዓሉ ሀገራዊ አንድነትና ሕብረ ብሔራዊነትን ሊያጠናክር በሚያስችል መልኩ እንደሚከበር ተገልጿል።