አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊ ዓየር ኃይል ለመገንባት በውጊያ መሰረተ-ልማት ግንባታ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን የዓየር ኃይል አባላት ገለጹ፡፡
በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች ዓየር ኃይሉን ሀገር የምትኮራበት ታላቅ ተቋም ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዓየር ኃይል አሁን ላይ በውጊያ መሠረተ-ልማት፣ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና አጠቃቀም በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቡን የተቋሙ የተለያያ ዲፓርትመንት ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዓየር ኃይል አስተማማኝ የሀገር መከታ በመሆን ለየትኛውም ግዳጅ አፈጻጸም ብቁና ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠው÷ ዓየር ኃይሉ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊ ተቋም የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡
በዓየር ኃይል አቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል የሮተሪ ዲፓርትመንት ዊንግ መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ኢንጂነር ሙሉቀን ደርሶ÷ ዓየር ኃይሉ የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ በሁሉም መስክ በዘመናዊ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዓየር ኃይሉ÷ ለውጊያ፣ መለማመጃና ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ አውሮፕላኖችን አስተማማኝ እድሳትና ጥገና በማድረግ ላይ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በዓየር ኃይሉ ቀደም ሲል የነበሩ አውሮፕላኖችን ወደ ዲጂታል የማሻሻያ ሥራ በማከናወን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
የዓየር ኃይል የከባድ ጥገና ማዕከል የምርምርና ልማት ክፍል ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ወንድማገኝ አርዓያ በበኩላቸው÷ ዓየር ኃይሉ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በማሻሻያ ሥራዎች ስኬታማ መሆኑን ገልፀዋል።
በከባድ የጥገና ማዕከል አውሮፕላኖችን የማዘመን፣ የዕይታና ዒላማ ዐቅማቸውን የማጎልበት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን ገልጸው÷ በቀጣይም ተጨማሪ ገቢዎችን ለማስገኘት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡
በዓየር ኃይል የአቪዬሽን ጥገና ማዕከል መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደረጄ አስታጥቄ÷ ዓየር ኃይል የውጊያ መሠረተ-ልማቶችን በመገንባት ያከናወናቸው ተግባራት ግዳጆችን በአስተማማኝ ብቃት መወጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በዓየር ኃይሉ የትራንስፖርት ሄሊኮፕተር ጥገና ስኳድሮን ኃላፊ ሻለቃ አንድነት ብርሃኑ እንዳሉት÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዓየር ኃይሉ በርካታ አመርቂ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በዓየር ኃይሉ የሄሊኮፕተር አብራሪዎቹ ሌተናል ኮሎኔል አየለ ዳዊት እና ሻለቃ ፀጋዬ አሰፋ በበኩላቸው÷ ዓየር ኃይሉ አሁን ላይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ይሁን በግዳጅ አፈጻጸም አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በአስቸኳይ ተልዕኮና ግዳጅ በቀንም ይሁን በሌሊት በመብረር ያሰብነውን ማሳካት የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!