Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለኢትዮጵያ አየር ክልል ዘብ የሆኑ ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራን በመሆኑ ኩራት ይሰማናል – የአካዳሚው መምህራን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ የሆኑና የላቀ የሙያ ብቃት ያላቸውን አብራሪና ቴክኒሻኖች እያፈራን በመሆኑ ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል ሲሉ የአየር ኃይል አካዳሚ አመራርና መምህራን ገለጹ።

የአካዳሚው ዲን ኮሎኔል ለማ ማሞ እንዳሉት÷ አካዳሚው ስመ-ጥር አብራሪዎችንና ቴክኒሺያኖችን በማፍራት የአየር ኃይሉ የሰው ኃብት ግንባታ የጀርባ አጥንት ሆኖ እየሠራ ነው።

ከለውጡ ወዲህ የአየር ኃይሉ የሰው ኃይል አቅም ግንባታና የሙያ ሥልጠናን በመገንባት ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

አየር ኃይሉ የአየር ክልሉን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠብቅ አብራሪዎችንና ቴክኒሺያኖችን ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የዋጁ እንዲሆን ሌት ተቀን እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በላይ የሚያኮራ ነገር የለም ያሉት ኮሎኔል ለማ÷ አየር ኃይሉ “የኢትዮጵያ ሰማይ አስተማማኝ ዘብ” ስለመሆኑ ገልፀዋል።

አየር ኃይሉን በ1981 የተቀላቀሉት ማስተር ቴክኒሺያን ግርማ ሮባ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋነኛ ትኩረት የሆነው የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በመሰማራት፤ ስመ-ጥር አብራሪዎችንና የጥገና ባለሙያዎችን እያፈሩ በመሆኑናቸው ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገርና ሕዝብ ደኅንነት የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰው÷ ከውጭ የሚመጣና ከውስጥ የሚፈትኑ ጠላቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት ሀገርን ከነክብሯ ማስቀጠሉንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የአቪዬሸን ኤሌክትሮኒክስ ክፍል ኃላፊ መቶ አለቃ ረቢራ እንድሪስ÷ አየር ኃይሉ ከለውጡ ወዲህ ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ ተሟልቶለት እየሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መቶ አለቃ ረቢራ፤ በአሁኑ ወቅት ለሀገራቸው ዘብ የሚቆሙ የአየር ኃይል አባላትን ለማፍራት በተሰማሩበት ሙያ በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

የሥልጠና ሥርዓተ-ትምህርቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት አመራሮቹ÷ ማሰልጠኛ አውሮፕላኖችና ሌሎች መሳሪያዎችም ዘመኑ የደረሰባቸው ናቸው ብለዋል።

Exit mobile version