Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከሕዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ቅድሚያ ለሠላም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሕዝቡ የሚነሱ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ቅድሚያ ለሠላም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡

የምክር ቤቱ 13 ቋሚ ኮሚቴዎች የሁለት ወር አፈጻጸም ከአስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በመሆን ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህ ወቅትም ለሁሉም ጉዳይ መሰረት የሆነው ሰላም ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባና ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ተናግረዋል።

ለዚህም ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የብሔራዊ ምክክር መድረክ ቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፥ በክትትልና ቁጥጥር ስራ የመጡትን ለውጦች በመገምገም ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲኖር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመግለጽ በቀጣይ የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚው በአግባቡ መድረሱን ማየት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት የኑሮ ውደነቱን ለመቀነስ የሚያግዙ በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በክትትልና ቁጥጥር ስራቸው እያንዳንዱ ተቋም ሰላምን በሚመለከት ሀገራዊ አስተሳሰብን መገንባት ላይ ምን እየሰራ ነው የሚለውን ማየት እንደሚገባም መገለጹን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version