Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሕዝቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው በጥራት መሥራት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት አንዲኖረውና ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በፍትሕ ጥራት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ።

በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ ሲካሄድ የነበረው የሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፥ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ቅሬታ ስላለው በሥርዓቱ ላይ የሚነሳውን የጥራት ችግር ለመቅረፍ ሕጋዊ አሠራርን የሚከተሉ የፍትሕ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኀብረተሰቡ በፍትሕ ተቋማት አገልግሎት እምነት ኖሮት እንዲመጣ ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ተደግፈው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ፥ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ያለው ማሻሻያ ወደ ኋላ እንዳይመለስና ውጤታማ እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ፥ በፍትሕ አካላት ላይ የሚነሳው እሮሮ የፍትሕችግር ብቻ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና ፀጥታ ችግር በመሆን ሕዝብና መንግሥትን እያራርቀ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንዳሉት ፥ ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ እምነት እንዲኖረው በየደረጃው ባሉ የፍትሕ አካላት የትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ሆኖም የክልል አመራሮች እየተባበሩ ባለመሆናቸው ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ አመራሮች ትብብር እንዲያደርጉ የክልል አፈ ጉባኤዎችን መጠየቃቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ፥ በዳኝነት በኩል ያለውን የሕዝብ እሮሮ ለማስቀረት የዳኝነት ነፃነትን በማይነካ መልኩ የፍትሕ ጥራትን ለማሻሻል በትብብር እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

#Ethiopia

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version