አዲስ አበባ፣ የካቲት 04፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በግርብርና እና በመሰረት ልማት ዘርፍ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ቤርዓኖ ወረዳ እየተሠሩ ያሉ የመስኖ ግብርና እና መሰረት ልማት ሥራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ በክልሉ በግርብርና እና በመሰረት ልማት ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በሶማሌ ክልል ሊታረስ የሚችል 10 ሚሊየን ሔክታር መሬት መኖሩን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው በመስኖ ሊለማ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በሸበሌ ዞን ቤርዓኖ ወረዳ በአርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶችና በመንግስት የለማው መሬትም ለዚህ ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ የሚገኘውን የመሬት ሃብት በአግባቡ በመጠቀም በምግብ እራስን የመቻል ሒደትን ማፋጠን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከመሰረት ልማት አንጻርም አሁን ላይ በክልሉ በፌዴራል መንግስት ብቻ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውሰጥ ከ700 እስከ 800 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው መንገድ ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ የተመረቀው የጎዴ ኡጋዝ ሚራድ አውሮፕላን ማረፊያም በጥራትም ሆነ በስፋት በሁሉም ክልሎች ከሚገኙት አውሮፕላን ማረፊያዎች እንደሚበልጥ አንስተዋል፡፡
የምንሰራው ፕሮጀክት ሰራን ለማለት ብቻ ሳይሆን÷ ዘመኑን የዋጀ እና ለተከታዩ ትውልድ የሚሻገር መሆን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በሶማሌ ክልል በግርብርና እና በመሰረት ልማት ዝርጋታ ዘርፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች ሰላምን መፈለግ እና ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ልዩነቶች ካሉም በውይይት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በጉልበት ማሳመን እና በጉልበት የመቀማት እሳቤ እንደማያዋጣ በመገንዘብ በንግግር ማመን እና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
የባንዳ ፍላጎት የሆነውን የመከፋፈል እሳቤና ሴራ በመተው አንድነትን እና ሕብረ ብሄራዊነትን የሚያጎላ አሰባሳቢ ትርክትን መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ