አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በግብርና፣ በኃይል ንግድ እና በባህል ትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በታንዛኒያ የሀዘን ጊዜ ደማቅ በሆነ አቀባበል በሀገራቸው የተቀበሉኝን ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉህን አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስምም በታንዛኒያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሊ ሀሰን ሙዊኒይ ህልፈት የተሰማኝን ሀዘን እገልፃለሁ ነው ያሉት፡፡
የዛሬው የሁለትዮሽ ውይይትም ለዛሬው ጠንካራ ግንኙነታችን መንገድ የከፈተውን ታሪካዊ ትስስራችንን ያመላከተ ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ በግብርና፣ በኃይል ንግድ እና በባህል ትብብር የተፈራረምናቸው የመግባቢያ ሰነዶች ለቀጠለው እና ተናባቢ ለሆነው የልማት ሥራችን መሰረት ናቸው ሲሉም ገልጸዋል በመልዕክታቸው፡፡