Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ያሳለፍናቸው የፈተና ጊዜያት ቀጣይ ምግባራችንና ተግባራችንን መቅረጽ አለባቸው – ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያሳለፍናቸው የፈተና ጊዜያት ቀጣይ ምግባራችን እና ተግባራችንን መቅረጽ አለባቸው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት እና በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል፡፡

የምክክር መድረኩ “ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት በመሻገር የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት÷ ክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ፈታኝ፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስተማሪ የሆነ ውስብስብ ፈተናዎችን አስተናግዷል፡፡

በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ችግር ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡

የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጸና በርካታ ሥራዎች ይጠይቁናል ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ የፖለቲካ አመራሩ በቁርጠኝነት እና በልበ ሙሉነት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

ክልሉ ከገጠመው የጸጥታ ችግር በተጨማሪ በበርካታ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የክልሉ ፈተናዎች ውስጣዊ እና ውጫዊ፤ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ናቸው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ “ያሳለፍናቸው የፈተና ጊዜያት ቀጣይ ምግባራችን እና ተግባራችንን መቅረጽ አለባቸው” ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው÷ በክልሉ የተፈጠረው ጽንፈኛ ኃይል የደቀነውን አደጋ የክልሉ መንግሥት ለመቀልበስ የሄደበት ብስለት የተሞላበት መንገድ በበጎነት የሚጠቀስ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የተከፈለው ዋጋ ውድ የሚባል ቢሆንም ክልሉን ከብተና መታደግ ተችሏል ያሉት አቶ ይርጋ÷ ችግሮችን መመርመር፣ ክፍተቶችን መለየት፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማመንጨት እና የቀጣይ ጊዜ ተግባራትን መንደፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የፖለቲካ አመራሩ ክልሉ የገጠመውን ውስብስብ ችግርና ፈተና በሚገባ ማጤን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

አንዱ የሌላውን ችግር መረዳት፣ ልምድ መቀያየር፣ መደጋገፍ እና መተጋገዝ ፈተናን ለመሻገር ምቹ መደላድል እንደሆነ ማስገንዘባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version