አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሩሲያ ሞስኮ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት እንደምታወግዝ አስታውቃለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግስት በሽብር ጥቃቱ ሰለባ በሆኑት ንፁሃን ዜጎች የተሰማውን ልባዊ ሀዘን የገለፀ ሲሆን÷ ለሩሲያ መንግስት እና ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል፡፡
ሽብርተኝነት ለሰው ልጆች ትልቅ አደጋ ነው ያለው መግለጫው መሰል የንፁሃን ዜጎችን ሞት ለመከላከል ሀገራት የጋራ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ከሩሲያ ጎን እንደሚቆም ገልፆ ሩሲያ አሸባሪዎችን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጧል፡፡
በሩሲያ መዲና ሞስኮ በተፈፀመ የጅምላ ተኩስ በርካቶች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
በጥቃቱ እስካሁን የ93 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን÷ ከ100 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸው ነው የተነገረው፡፡

