Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የለውጡ መንግስት ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመንቀልና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ሲሰራ ቆይቷል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የለውጡ መንግስት ባለፉት የለውጥ እና የብልፅግና ጉዞ አመታት ስር የሰደዱ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመንቀል፣ የተረጋጋ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር አልሞ ሲሰራ ቆይቷል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ያለፉት 6 ዓመታት የነበረውን የለውጥ ጉዞ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የለውጡ መንግስት ሁሉንም የሚያሳትፍ፣ የሚያግባባ፣ የሚያስተሳስር፣ አብሮነትን በትብብር መንፈስ የሚያጎለብት፣ ብዝሃነትን እና አንድነትን የሚያሳልጥ በብሔራዊ ትርክት ላይ የተመሰረተ ሀገረ መንግስት እየገነባ ይገኛል ብለዋል፡፡

ያለፉ ቁርሾዎች እና ስብራቶችን የሚጠግን የሽግግር ፍትህ ለመተግበር የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

ልዩነቶችን እና የማያግባቡን ጉዳዮችን በውይይት እና ሰጥቶ መቀበል፣ በድርድር ለመፍታት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ተሳትፎ እና አካታችነትን ለማጎልበትም በርካታ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉ ገለልተኛ እና ነፃ ተቋማትን እንድትገነባ መሰረት ጥሏል ብለዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ነፍጥ ያነሱ ሃይሎች ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያቀርቡ የሰላም በር ለሁሉም ተከፍቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ጀምሮ የይቅርታ እና የምህረት እሳቤ በተጨባጭ እንዲተገበር በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውንም አንስተዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመንቀልና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በእምነት ተቋማት መካከል የነበሩ ችግሮች በድርድርና በሽምግልና እንዲፈቱና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበቡ አሳሪ ህጎች እንዲሻሻሉ መደረጉን እንዲሁም ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መሰረት መጣሉን አስታውሰዋል።

ኢኮኖሚውን ከፍፁም ውድቀት እና ስብራት መታደግ፣ የውጭ እዳ ክምችት ችግር የታደገ የኢኮኖሚ ሪፎርም መከናወኑን እንዲሁም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውጫዊ እና ውስጣዊ ተፅዕኖዎችን በመቋቋም የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት በእጥፍ እንዲያድግ የለውጡ መንግስት መስራቱን ገልጸዋል።

የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም እንዲያድግ እንዲሁም ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከነበሩበት ችግሮች ተላቀው ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ አድርጓል፡፡

እንደነ ኮይሻ ያሉ ደግሞ ከነበረባቸው ችግሮች ተላቅቀው ዛሬ ግንባታቸው በመፋጠን ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version