አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝብ ተናግሯል፤ መንግሥትም ያዳምጣል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷የለውጡን 6ኛ ዓመት በማስመልከት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቀናት የድጋፍ ሰልፎች መካሄዳቸውንና በቀጣይም በቀሪ አካባቢዎች እንደሚካሄዱ አንስተዋል፡፡
በሰልፎች ህዝቡ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲቀጥል፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና መንግሥታዊው አስተዳደር በሃላፊነት እንዲሰራ ያለውን አቋም መግለጹን ተናግረዋል።
ህዝቡ ለውጡ ያመጣለትን የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች በማናቸውም ሁኔታ በሚፈጠሩ ችግሮች አሳልፎ እንደማይሰጥ አረጋግጧልም ነው ያሉት።
መንግስት የህዝቡን ድምፅ ሰምቷል ያሉት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷የህዝቡ የሰላምና ደኅንነት፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የወሰንና የማንነት፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጥያቄዎቹን በሕግና በሥርዓት ለመፍታት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከለውጡ ጎን በመቆም ላሳዩት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡