አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሙሌት እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሶስትዮሽ ውይይት ተካሄደ።
በበይነ-መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በታዛቢነት በተገኙበት ነው በትናትናው ዕለት የተካሄደው።
በዚህ ስብሰባ ሀገራቱ የድርድር ስነ-ስርዓትን ፣ ታዛቢዎችን ሚና፣ ስለ ድርድሩ አካሄድ እና ባልተቋጩ ዋናዋና ድርድር ጉዳዮችን በተመለከተ ተነጋግረዋል።
እንዲሁም እያንዳንዱ ሀገር ዋና ዋና የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህም መሰረት በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የታዛቢዎቹ ሚና ምን ይሁን የሚለውን በተመለከተ በሀገራቱ መካከል መግባባት ላይ ያልተደረሰ ሲሆን ስብሰባው በዛሬው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል።
የሶስቱ ሀገራት ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ ናት ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

