አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት አበረታች መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለፁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጽጥታ ኮሚሽነር ከሆኑት አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬን ጋር ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።
አምባሳደር ታዬ ÷የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ተግባራዊ የተደረገውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ በወቅቱ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ባንኮሌ ÷ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው ፥ በተለይም የታጠቁ ኃይሎችን ትጠቅ የማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ሂደት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረት ከሰላም ፈንድ ቋቱ የ1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ከዚህ ማዕቀፍ የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ አባል ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ህብረቱ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ማሰማራቱ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኝነቱን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
አክለውም ፥ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ የማዳበርና ማስፈጸም ስራዎችም ህብረቱ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ወሳኝ በሆኑ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ባንኮሌ÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ማስፈን ጥረቶች ውስጥ ወሳኝና ውጤታማ ሀገር እንደሆነች ተናግረው ፥ ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግ አንስተዋል።