አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ትናንትም ቀጥሎ ውሏል።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ በድርድሩ ሁለት የቴክኒክና የህግ ቡድኖች ቢኖሩ በሚል ያቀረበችውን ሀሳብ ሱዳን መቀበሏን አመልክቷል።
በግብፅ በኩል ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሳትቀበለው የቀረችውን ረዘም ያለ የድርቅ ጊዜን እና ደረቃማ ዓመትን በተመለከተ ዝርዝር ህግ መኖር አለበት የሚለውን ሃሳቧን በድጋሚ አንስታለች።
በእለቱ በነበሩ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደ ድርድር ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ባቀረበችው ሃስብ ላይ ንግግር መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ዙር የግድቡን የውሃ አሞላል እና አሞላሉ የሚገዛበት መመሪያን በተመለከተ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሃሳብ ለመቀጠል ከመግባባት መደረሱን ነው ያመለከተው።
ረዥም ድርቅን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴ የውሃ አለቃቁ ላይ ህግን እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት እንዲሰጠው እና ዝርዝር አለቃቀቅን በተመለከተ ግን ድርድር እንደሚያስፈልግ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
እንደዚሁም የግድቡን ደህንነት የተመለከተ ህግ እና ግድቡ በሚኖረው አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ጥናት ማስፈለግ ላይ ተግባብተናልም ነው ያለው መግለጫው።
የግብፅ ተደራዳሪዎች በእለቱ የነበራቸው ተሳትፎ የተቀዛቀዘ ነበር ያለው መግለጫው፥ ከተራዘመ የድርቅ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ፍላጎት በማሳወቁ ላይ ብቻ መሳተፋቸውን አመልክቷል።
ሆኖም በመጨረሻ ሰዓት የግብፅ ተደራዳሪዎች ውይይት ሲደረግበት በነበረው እና ከዚህ በፊት ራሳቸው ሊያሰራ የሚችል ሰነድ ነው ብለው አስተያየት የሰጡበትን ሱዳን ያቀረበችውን ሰነድ መልሰው ተቃውመዋል።
በተጨማሪም የራሳቸውን አቋም ይዘው እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን የተቃወሙት ግብፃውያኑ፥ ድርድሩ እየተካሄደ የግድቡ ውሃ ሙሌት ሊካሄድ አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።
እንደዚሁም እየተካሄደ ያለው ድርድር ሰኞ እንዲጠናቀቅ እና እስካሁን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያስቀመጧቸውን ብድርድሩ ለተገኙ ለውጦች እውቅና ላለመስጠት ፍላጎት ታይቶባቸዋል ነው ያለው።
ድርድሩ ዛሬም እንደሚቀጥል የጠቆመው ሚኒስቴሩ የተደረጉ ድርድሮችን መሰረት በማድረግ በተዘጋጁ መመሪያዎች እና ህጎች ላይ ሀሳብ ይለዋወጣሉ ብሏል።
ነገም በእስካሁኑ ድርድር የተገኙ ለውጦችን በመገምገም ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ድርድሩ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሆኖም ግን በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ቀጥሎ ባለበት ወቅት የግብፅ የውሃ ሀብት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በትናንትናው እለት “በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች በኢትዮጵያ ምክንያት እየተስተጓጎሉ ነው” የሚል መግለጫ መሰጠቱን ሰምተናል ያለው ሚኒስቴሩ፥ እውነታው ግን ኢትዮጵያ ድርድሩ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ እያደረገች ነው፤ አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር ከተደናቀፈም በግብፅ ምክንያት ነው ብሏል ሚኒስቴሩ።
ምክንያቱም ግብፅ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋፈስ ሀገራት የአባይን ውሃ ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብትን የሚጋፋውን በቀኝ ግዛት ዘመን የተፈረመው ስምምነት ላይ ሙጥኝ ብላ በመቅረቷ ነው ብሏል በመግለጫው።
እየተካሄደ ያለው ድርድር በአባይ የውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ አለመሆኑን ያስታወቀችው ኢትዮጵያ፥ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና ዓመታዊ የስራ ክንውን በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር በሚፈረም መመሰሪያ መሰረት እንደሚካሄድ እና ይህም የህዳሴ ግድብ በአውሮፓውያኑ በ2015 በሶስቱ ሀገራት የስምምነት መርሆዎችን በተከተለ መልኩ የሚተገበር መሆኑን አስታውቃለች።
ከዚህ በዘለለ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር እና ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ ስምምነቶችን እድትቀበል የሚደረጉ ጫናዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው በማሳወቅ፤ ሀቀኛ፣ መተማመን የሰፈነበት እና ግልፅ የሆነ ድርድር ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ እንዲቋጭ እንደሚረዳም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን አቋም አንፀባርቋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

