አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብፅ የአባይን ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ግትር አቋም ደግም ለተጀመረው ድርድር እንቅፋት መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አምስተኛ ቀኑን በያዘው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የሶስትዮሽ ድርድር የእስካሁን ውጤት ላይ እየሰጡት ባለው መግለጫ የግብፅ የእኔ ጥቅም ብቻ ይጠበቅ አቋም ድርድሩን እየተፈታተነ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፥ ግብፅ በድርድሩ በተለመደው ሁለት አካሄዷ ቀጥላበታለች ነው ያሉት።
ግብፅ አንድ እግሯን ድርድሩ ላይ አንድ እግራን የፀጥታው ምክር ቤት አስቀምጣ መደራደርን መምረጧን በማንሳት።
በድርድሩ ግብፃውያኑ የፈለጉት እና የጠየቁት ሁሉ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ የሚሰጡት ግን የላቸውም ነው ያሉት።
ግብፅ የጋራ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ ውሃ መሙላት አትችልም የሚል ተቀባይነት የሌለው ሃሳብ ይዛ መቀጠሏም ተነግራል።
ኢትዮጵያ አሁንም የአባይ ባለቤትም ዋነኛዋ የመፍትሄው ወሳኝ ሀገር እንደመሆኗ ግብፅ ሁሌም ላለመስማማት ራሷን ያዘጋጀች ቢሆንም መፍትሄው ውይይት እና ድርድር እንደሆነ እንደምታምን ነው አቶ ገዱ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ሰላም እና ልማት የግብፅን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም አያረጋግጥም፤ የግብፅ መንግስታት ግን ይህን መረዳት ሲሳናቸው ተስተውሏል የሚሉት አቶ ገዱ፥ ምንም ሳይሰጡ ግን የሌሎችን ጠቅልሎ የመውሰድ አባዜያቸው እንዳልለቀቃቸው ይናገራሉ።
ከወደ ካይሮ የሚታየው የበዛ ስስት በድርድሩ ላይ እንቅፋት መፍጠር መቀጠሉን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የጋራ ልማት ፍላጎት እና የግብፅ ባለስልጣናት ፍላጎት ለየቅል መሆኑ ፈተናነትን ያብራራሉ።
የግብፅ መሪዎች የኢትዮጵያ ለዘመናት በጨለማ ውስጥ መቆየት እንዴት ሊያስደስታቸው ይችላል ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሀገሪቱ በ2015 በካርቱም የተፈረመውን የመርህ ስምምነት ለማፍረስም ጥረቷን ቀጥላለች የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ግብፅ ከመርህ ስምምነቱ ባለመውጣት እና የሶስትዮሽ ድርድሩን በመቀጠል ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የአባይ ውሃ አጠቃቀም የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት ባይ ናቸው።
የካይሮ አካሄድ ግን ከዚህ በተቃርኖው ነው እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ሊረዳ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በዳዊት መስፍን እና ፋሲካው ታደሰ

