አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያየዘ መንግሥት ለመመካከር፣ ለመወያየት እና ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ”ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በኮንፈረንሱ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ክልል ም/ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
አቶ አረጋ ከበደ በኮንፈረንሱ ባደረጉት ንግግር÷ የክልሉ ሕዝብ የማኅበራዊ ትስስር ገመዶች የተበጠሱበት እና የከፋ ጉዳት የደረሰበትን ከባድ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኝ በመሆኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሁሉም ማኅበረሰብ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
የሰላም ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችም ለክልሉ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ይጠቅማል የሚሉትን ሃሳብ ከአሉባልታ በጸዳ መንገድ በማቅረብ የገጠመውን የሰላም እጦት ችግር ብቻ ሳይሆን የመፍትሄ መንገዶችን በሚያመላክት መንገድ በጎ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የገጠመንን ችግር ምንነትና መንስኤውን፣ የፈጠረውን አሉታዊ ውጤት መረዳትና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ስልቶችን መንደፍ በኮንፈረንሱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የታጠቁ ሃይሎች ወደ ሰላምና ውይይት እንዲመጡ ለሚፈለገው የሰላም አማራጭ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከኮንፈረንሱ የሚጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሰላም፣ በንግግርና ውይይት አማራጭ እንጂ በሃይል ምንም አይነት ለውጥ እንደማይመጣ አውቀን ለሰላምና መረጋጋት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው÷ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ የአማራ ሕዝብ ጽኑ ፍላጎት እንደነበረውና ለውጡንም እንዳሳካ ሁሉ ዛሬም ለሰላሙ በመረባረብ ወደ ልማቱ በሙሉ አቅሙ መመለስ ይኖርበታል ብለዋል።
መገዳደልና መጠፋፋትን ካላስቆምን ማንም ማሸነፍ አይችልም፤ የትም የሚያሻግር እድገትም አናይም ያሉት አፈ ጉባዔው÷ የሰላም በር ተከፍቶ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ አስተዋጽኦ እንዲያስቀጥል ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም ይጠበቅብናል ብለዋል።
ለመመካከር፣ ለመወያየትና ለንግግር መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ደጋግመን ተናግረናል፤ ስለሆነም ሕዝቡ ትልቅ ሃላፊነት አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የሰላም ኮንፈረንሱ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ሲካሄድ የቆየው ማጠቃለያ ኮንፈረንስ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ

