አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የዋይት ሀውስ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ላይ ይገኛሉ።
የዋይት ሀውስ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት በትናንትናው እለት በትዊተር ገጹ፥ “257 ሚሊየን የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች የኢትዮጵያ ጠንካራ አመራርን ለማየት ይሻሉ፤ ይህም ማለት ፍትሃዊ ስምምነትን የሚጠይቅ ነው፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ የቴክኒክ ጉዳዮች መፍትሄ አግኝተዋል፤ አሁን ደግሞ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ የሚደረስበት ጊዜ ሊሆን ይገባል” ፅሁፍ አውጥቷል።
257 million people in east #Africa are relying on #Ethiopia to show strong leadership, which means striking a fair deal. Technical issues have been resolved – time to get the GERD deal done before filling it with Nile River water!
— NSC (@WHNSC) June 17, 2020
መልእክቱም ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙርያ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ሙሌት እንዳትጀምር የሚል እንድምታ ያለው ሆኖም ተገኝቷል።
ታዲያ ምክር ቤቱ በትናንትናው እለት የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ ሲሆን፥ ኢትዮጵያውያኑ ተቃውሞዋቸውንም በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያኑ የዋይት ሀውስ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጥስ መሆኑን በመግለፅ፤ “ምን ማድረግ እንዳለብን ማንም አይነግረንም፤ በድንበራችን ውስጥ ያለን ግድብ ውሃ ለመሙላት ማንንም አንጠይቅም” ያሉ አስተያየት ሰጪ ኢትዮጵያውያን አሉ።
86 በመቶ የናይል ውሃ ምንጭ ኢትዮጵያ ሆና ሳለ፣ ከ60 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ ኤሌክትሪክ በማያገኙበት ሁኔታ ግብፅ ግን ቅንጣት ታክል ውሃ ሳታበረክት ከህዝቦቿ ውስጥ 98 በመቶዎቹን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ባደረገችበት ሁኔታ የምታሰማውን ጭሁት የምትጎነጉነውን ሴራ ማስቆም ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።
100 በመቶ በኢትዮጵያውያን ወጪ የሚገነባን ግድብ ውሃ ሙሉ አትሙሉ ማለት የሚችል አካል የለም ያሉት ኢትዮጵያውያኑ፤ የግድቡ የመጀመሪያ ውሃ የመያዝ ሂደት ስምምነት ላይ ቢደረስም ባይደረሰም ግድባችን ይሞላል የሚል አስተያየት አስፍረዋል፤ በራሳችን ግድብ ለማንም ፈቃጅና ከልካይ ፍላጐት የምንተወው አይደለም በማለት።
ኢትዮጵያ ውሃውን በፍትሃዊነት ለመጠቀም ሲባል ከግብፅ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ረጅም ርቀት መጓዛንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ይህን ያክል ርቀት የተጓዘችው በጋራ ጥቅም ስለምታምን መሆኑንም በመግለጽ፤ “ግብፅ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበላትን ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሄን እድንትቀበል ምከሯት” ያሉም አሉ።
ግብፅ በእረግጥ የቸገራት ውሃ ሳይሆን የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም መጉዳት መሆኑን የጠቀሱ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ በግብፅ ያለውን እምቅ የከርሰ ምድር ውሃ፣ አባካኝ የውሃ አጠቃቀም ባህል እና ሌሎች ማስረጃዎችን በማጣቀስ የሀገሪቱን ሴራ ያጋለጡም ኢትዮጵያውያን አሉ።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

