አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል እና አዲሱ የሲዳማ ክልል በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ፊት ቀርበው የስልጣን ርክክብ አካሄዱ።
የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ የሲዳማ ዞን በክልል እንዲደራጅ በዛሬው እለት ወስኗል።
ምክር ቤቱ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ጉባኤ የሲዳማ ዞን በክልል እንዲደራጅ የወሰነው የሥልጣን ርክብክብ እንዲደረግ የቀረበለትን አጀንዳ ላይ ከተወያየ በኋላ በማጽደቅ ነው ።
በቀረበው ሰነድ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ርስቱ፥ የሲዳማ ክልል እራሱን ችሎ በመውጣቱ በሌሎች ህዝቦች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
የህዝቦች አብሮነት ከዚህ ቀደምም ለረጅም ዓመታት ተጠናክሮ የቀጠለ ነው ያሉት አቶ እርስቱ ነባሩ ክልል እና አዲሱ ክልል በመደጋገፍ ለጋራ እድገት እንሰራለን ብለዋል።
ውይይቱን ተከትሎም የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ዞን በክልል እንዲደራጅ የቀረበለትን አጀንዳ አፅድቋል።
ውሳኔውን ተከትሎ ሲዳማ በሀገሪቱ 10ኛው ክልል የሚሆን ሲሆን፥ የምክር ቤቱ አባላት ለሲዳማ ክልል ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በክልሉ ሌሎች አካባቢዎችም እየተነሱ ያሉ የመዋቅር ጥያቄ በተገቢው መልኩ እንዲታይ መንግስትና የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ።
ከዚህም ሌላ ምክር ቤቱ የ2012 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊየን 600 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ረቂቅ በጀት ላይ በመምከር አጽድቋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

