አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዓለም ላይ የተከሰተውን የኮቪድ19 ወረርሽኝ ለመግታት የቻይና አፍሪካ ትብብር የማይተካ ሚና እንዳለው ተናገሩ።
ትናንት “ዓለም አቀፉ የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ኢኒሸቲቭ” የቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ19 ወረርሽኝ ለመግታት በቻይና እና አፍሪካ መካከል የሚደረገው ትብብር ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ መሆኑን አቶ ገዱ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
ቻይና የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት የተከተለችውን ስትራቴጂ እና የተገኘውን ውጤትም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ የቻይና መንግስት እና እንደ ጃክማ የመሳሰሉ የቻይና በለሃብቶች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት አቶ ገዱ፥ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የቪዲዮ ኮንፈረንሱ የኮቨድ19 ወረረሽኝ በታዳጊ ሃገራት ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
“የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ኢኒሸቲቭ” ዓለም አቀፍ ትብብርን በማሳደግ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በተመለከተ በስፋት መብራራቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

