Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለቴክኖሎጂ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል- ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቴክኖሎጂና ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት መሰጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ያለማቸውን የንብረት፣ የሰው ኃይልና የፕሮጀክት አስተዳደር የዲጂታል ስርዓትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ÷ ኢትዮጵያን ከልመና ለማላቀቅና የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ለግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ለቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

የአማራ ክልል በግብርናው መስክ ለሀገር ዕድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው በመግለጽ ፤ በቱሪዝም ዘርፉም ከነባር ቅርሶች ባሻገር እንደጎርጎራ ያሉ ውብ መዳረሻዎች መገንባታቸው ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የንብረት፣ የሰው ኃይልና የፕሮጀክት አስተዳደርን ለማዘመንና ስራን ውጤታማ ለማድረግ ያስጀመራቸው የአይሲቲ መሠረተ ልማቶች የሚያበረታቱ ናቸው ብለዋል።

የለሙ መሠረተ ልማቶችን ከዘራፊዎችና ከሳይበር ጥቃት መከላከል የግድ እንደሆነም ጠቁመው ፤ ከሌሎች ተቋማት ጋር የተናበበ አገልግሎትን መዘርጋትም አስፈላጊ እንደሆነ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ በቴክኖሎጂ ለተደገፈ ዘመናዊ አሰራር ያሳየው ተነሳሽነት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው ÷የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ የቴክኖሎጂ ልማት ነው ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ያስጀመራቸው የዲጂታል አገልግሎቶች በተለይ የህዝብ የአገልግሎት እርካታን ለማሻሻል የጎላ አበርክቶ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው በአግባቡ ውጤት እንዲያመጣ የሰው ኃይል ሙያዊነት እውቀትና ስነ-ምግባር ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት።

የዲጂታል አገልግሎቱ የህዝብን ቅሬታ የፈታ መሆኑን በየጊዜው መፈተሽ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው ፥ በ2017 ዓ/ም በሁሉም ዘርፎች ዲጂታላይዜሽንን ለመተግበር መስራት እንደሚገባም አንስተዋል።

Exit mobile version