Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል የሚደረገው ድርድር እንደቀጠለ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል የሚያደርጉት ውይይትን እንደቀጠለ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ የናይል ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመጣ ያድረገችበት መንገድ ትልቅ ስኬት እንደነበረ ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በሶስቱ ሀገራት መካከል አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር እንደቀጠለ በመግለጽ፤ ድርድሩ እደተጠናቀቀ የተገኙትን ውጤቶችና አጠቃላይ ሁኔታውን በሚመለከተው አካል በኩል ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ የሚቀጥል መሆኑንም አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የፊት ለፊት የውይይቶች የቀነሱ ቢሆኑም በቨርችዋል ዲፕሎማሲውን አጠናክሮ መቀጠሉን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታውቅዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው፥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከአህጉራዊ ድርጅትና ተቋማት ተወካዮች ዲፕሎማሲያው ስራዎችን እየከወኑ ነው ብለዋል።

በዚህም ከስዊድን፤ ከሩሲያ፤ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከሌሎችም ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ነው አምባሳደር ዲና የገለፁት።

በተጨሪም ከቻይና ከጣሊያን እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

መንግስት የጀመረውን የዜጋ ተኮር የውጭ ዲፕሎማሲ ግንኙነት አጠናክሮ የቀጠል ሲሆን፥ የኮቪድ 19 መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በሙሀመድ አሊ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version