አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት ቀጣይነት ባለው ትብብር መጠናከር እንዳለበት በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ዡ ቢንግ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ዡ ቢንግ ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ጌዲዮን (ዶ/ር) በውይይታቸው ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮ-ቻይና ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጠንካራ እና የማይናወጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በምታደርገው እንቅስቃሴ ቻይና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንድታደርግም መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ (ፎካክ) ማዕቀፍ ከተቀመጡት ዓላማዎች ጋር ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዋን እንዳናበበች አስምረውበታል።
አምባሳደር ዙ ቢንግ፥ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ባለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ስኬቶችን በመግለጽ፤ አጋርነቱን ቀጣይነት ባለው የትብብር ጥረት ማጠናከር ስላለው የጎላ ሚና አብራርተዋል፡፡