አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግንባታቸው ሳይጠናቀቁ በተተከሉ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት የጀመሩትን የሕዳሴ ግድብና የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ጨምሮ 19 ማመንጫ ጣቢያዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተመላከተ፡፡
እነሱም ቆቃ፣ አዋሽ II፣ አዋሽ III፣ ፊንጫ፣ መልካ ዋከና፣ ጢስ ዓባይ II፣ ግልገል ጊቤ 1፣ ተከዜ፣ ግልገል ጊቤ II፣ በለስ፣ አመርቲ ነሽ፣ አሽጎዳ፣ አዳማ I፣ አዳማ II፣ ግልገል ጊቤ III፣ ረጲ፣ ገናሌ ዳዋ 3፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና አይሻ II መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የኃይል ማመንጫዎቹ ከ1952 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ወደ ሥራ መግባታቸውን እና በዓመት 6 ሺህ 879 ሜጋ ዋት ወይም 23 ሺህ 59 ጊጋ ዋት ሠዓት የማምረት አቅም እንዳላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ማናጀር ፍስሐ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የሕዳሴ እና የአይሻ II የማመንጨት አቅምና ዓመታዊ የኃይል ምርት ለጊዜው አሁን ወደ ኦፕሬሽን በገቡ ተርባይኖች እየመነጨ ያለውን ብቻ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል ጢስ ዓባይ I፣ አሉቶ ላንጋኖ እና አባ ሳሙኤል በአሁኑ ወቅት ኃይል ማመንጨት ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም የአይሻ፣ አሰላ፣ የሕዳሴ ግድብ እና ኮይሻ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ አሉቶ የእንፋሎት ማስፋፊያ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በከፊል ኃይል ማመንጨት የጀመሩትን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ አይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ ኮይሻ የውኃ ኃይልና አሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በዓመት 7 ሺህ 240 ሜጋ ዋት ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህም አሁን ያለውን 5 ሺህ 656 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ከ12 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ከፍ እንደሚያደርገው ነው ያመላከቱት፡፡
በዮሐንስ ደርበው

