Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ግብጽ የምታሰማውን የተዛባ ትርክት ለመቀየር ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ይከናወናል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ )ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ላይ እያሰማች ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የስራ አስፈጻሚ አባላት ትናንት ባካሄዱት መደበኛ ስብሰባ ግድቡ ከኃይል ምንጭነት በተጨማሪ የወንዙን ጂኦ ፖለቲካ የቀየረ መሆኑ ተገልጿል።

የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ግብጽ በግድቡ ዙሪያ እያከናወነች ያለውን የተዛባ ትርክት ማስተካከል እንደሚገባ አንስተዋል።

ግብጽ ግድቡን ዓለም አቀፍ የጸጥታ ስጋት አድርጋ በማቅረብ በተለይ የዓረብ ሃገራትን ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሰራች መሆኑም ተገልጿል፡፡

ስለ ግድቡ የሚደረጉ የተግባቦት ስራዎችን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በመምራት የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም ለዓለም ማሳወቅ እንደሚገባም ነው አባላቱ ያስገነዘቡት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በዓለም ላይ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች ተሞክሮ የሚያሳየው የላይኛው ተፋሰስ ሃገራት ወንዙን በመጠቀም ደረጃ የተሻለ ዕድል እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የያዘችውን ሃቅ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳቱ ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጓዳኝ በግድቡ ዙሪያ ጠንካራ ሃገራዊ አንድነት ለመፍጠር መሰራት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

ግድቡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ አንጻር የግድቡን ደህንነት የሚያስጠብቁ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ግድቡ ይዟቸው የመጡ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመጠቀም ከወዲሁ በተደራጀ መልኩ እንዲሰራም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version