አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ 90 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የኦሮሚያ ክልል መንግስት በጀትን አፀደቀ።
ጨፌ ኦሮሚያ 12ኛ መደበኛ፣ 5ኛ ዓመት 5ኛ የሥራ ዘመን ጉባዔውን በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ጨፌ ኦሮሚያ በዛሬው እለት ቀጥሎ ባካሄደው በመደኛ ስብሰባውም የ2013 የክልሉ መንግስት በጀትን ረቂቅ በጀትን ተመልክቷል።
ጨፌ ኦሮሚያ 90 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የኦሮሚያ ክልል መንግስት በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
በተጨማሪም ጨፌ ኦሮሚያ የ2012 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀትን ከተመለከተ በኋላም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በመቀጠልም ጨፌ ኦሮሚያ በመደበኛ ስብሰባው የቀረቡለትን የተለያዩ አመራሮችም ሹመትም ተቀብሎ አጽቋል።
በዚህም መሰረት፦
1 . ዶክተር መንግስቱ በቀለ፥ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ
2. አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፥ የኦሮሚያ መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ
3. ወይዘሮ መስከረም አበበ፥ የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር
4. አቶ አህመድ ሰይድ ኡመር፥ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ
ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል።
ጨፌ ኦሮሚያ በመቀጠልም በተለያዩ ምክንያቶች በተጓደሉ ሶስት የፌዴሬሽን አባላት ምክትም አዳዲስ አባላትን መርጧል።
በዚህም መሰረት፦
1 . አቶ ፍቃዱ ተሰማ
2 አቶ ሳዳት ነሻ
3 አቶ አብዱል ሀኪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል።
እንዲሁም ጨፌው በተለያዩ ምክንያቶች በተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ምትክም አቶ ጀግናው ግዛው፣ ወይዘሮ ሽታዬ ለማ እና ወይዘሮ ሲቲና በዳሶን መርጧል።
ተሿሚዎችም በጨፌ ኦሮሚያ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
ጨፌ ኦሮሚያ በዛሬው የጉባኤው ውሎው የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2012 አፈጻጸምን ገምግሟል።
በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ አገለግሎት ረቂቅ አዋጅንም ከተመለከተ በኋላ አጽድቆታል።
በሙለታ መንገሻ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

