አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ከባቢን መገንባት እና የሳይበር ስጋቶችን መከላከል ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞና ውጥኖች ላይ ያተኮረ ኤግዚቢሽን እና ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል።
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ከባቢን መገንባት እና የሳይበር ስጋቶችን መከላከል ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የመጨረሻ ዓመት ላይ እንገኛለን በማለት ገልጸው፤ በስትራቴጂው የባለፉት የትግበራ ጊዜያት በርካታ ስኬቶች መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፤ ይህንንም መነሻ በማድረግ የቀጣይ 5 አመታት “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ” መዘጋጀቱን መጠቆማቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬት ወሳኝ የሆኑትን “የዲጂታል መንግስት ስትራቴጂ” እና “የኤሌክትሮኒክ ንግድ ስትራቴጂ” ረቂቆች ይፋ አድርገዋል።