አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከሞሮኮው ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ (አር ኤን አይ) ፓርቲ ተወካይ መሐመድ ሳዲኪ (ፕ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አደም ፋራህ በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመታደም ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ የገቡትን መሐመድ ሳዲኪ (ፕ/ር) በዛሬው ዕለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም÷ የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጽናት ለቀጣይ ቁርጠኝነትን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምፅ መሆኑን በተግባር ማሳየቱንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲመዘገብ፣ የህዝቦች አንድነትና ትብብር እንዲጎለብት ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው÷ በፓርቲ ደረጃ ያላቸው ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
መሐመድ ሳዲኪ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያና ሞሮኮ በታዳሽ ሀይል፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
የደቡብ ደቡብ ትብብር፣ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን በማጠናከር በተፈጥሮ ሀብትና ሌሎች ዘርፎችም በጋራ እንሰራለን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ በሞሮኮ የሥራ ጉብኝት እንዲያደርግ ግብዣ በማቅረብ እንደ ፓርቲ ያላቸው ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።