አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን እንዲሁም ዲፕሎማቶችን ያሰባሰበው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን አግኝቷል፡፡
ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ የተካሄደው ዓመታዊ የመሪዎች ጉባኤ በርካታ ሐሳቦችን፣ የጎንዮሽ ውይይቶችን እና የቀጣይ የጋራ አጀንዳዎች ላይ መክሮ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
ይህንን አኅጉራዊ ኩነት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ለአፍሪካ ቅድሚያ የሰጡ ሀገራት ብሄራዊ ጥቅሞቻቸውን ከአፍሪካ ሀገራት የጋራ ራዕይ ጋር ለማሰናሰል የኅብረቱን አጀንዳዎች በሚዲያዎቻቸው የፊት ገፅ አስፍረዋል፡፡
ከነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ የሆነው የቱርኩ አናዶሉ ኤጀንሲ÷ ጉባኤው በአኅጉሪቱ ያለውን ሰላም እና ጸጥታ ለማረጋገጥና በሀገራት ዘንድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ዘግቧል፡፡
የመሪዎቹ ጉባኤ ቀጣናዊ ተቋማትን ለማሻሻል የጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆኑን ጠቅሶ÷ ይህም የኅብረቱ ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የቻይናዎቹ ዥንዋ አና ሲጂቲኤን “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደው የህብረቱ ጉባኤ÷ በአይነቱ ለየት ያለና በርካታ መሪዎች የተገኙበት እንደነበር ዘግበዋል፡፡
ጉባኤው የአጀንዳ 2063 አካል የሆነውን አኅጉራዊ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ ለማድረግ ተጨባጭ ምክክሮች ተካሄዱበት መሆኑን እንዲሁም በአኅጉሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን ለመፍታት የጋራ አቋም የተወሰደበት እንደነበር አመላክተዋል።
የፖለቲካ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ክራይስስ ግሩፕ÷ ኅብረቱ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት በተመለከተ ውይይት ማድረጉን እና ይህም የሱዳንን ቀውስ ሊፈታ እንደሚችል በዘገባው አስፍሯል፡፡
የአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ፣ የሳህል ቀጣና ጉዳይ፣ የካሜሩን ምርጫ፣ የደቡብ ሱዳን ሰላም፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጉዳይ የኅብረቱ አጀንዳዎች እንደነበሩም ዘግቧል፡፡
የአሜሪካው ቪኦኤ እና የጀርመኑ ዲ ደብሊው በበኩላቸው ጉባኤውን በተመለከተ በሰሩት ትንታኔ÷ የኅብረቱ ጉባኤ በአህጉሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን ለማስቆም ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
የሩሲያውዎቹ ስፑትኒክ እና አር ቲ፣ አፍሪካ ኒውስ፣ ቢቢሲ፣ ፍራንስ 24፣ አሬብ ኒውስ፣ አፍሪካ ኒውስ፣ ሬውተርስ፣ ሲኤንኤን፣ ዘ ኢንዲፔንደንት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለጉባኤው ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል።
ለመሪዎች ጉባኤ አስቀድማ ለወራት ዝግጅት ስታደርግ የነበረችው አዲስ አበባም 38ኛውን የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ በማስተናገድ መሪዎችን እየሸኘች ትገኛለች፡፡
ከኅብረቱ ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተለያዩ መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ