Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ያለመ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ታዳሽ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከመላው አፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት መድን ድርጅት የአፍሪካ ንግድ መድን ኤጀንሲ (ኤቲአይዲአይ) ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመች፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ታዳሽ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመሳብ የምታደርገውን ሽግግር ያፋጥናል መባሉን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ የስምምነቱ መፈረም ዘርፈ-ብዙ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ለታዳሽ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የኤቲአይዲአይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማኑኤል ሙሴ በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የሀገሪቱን የታዳሽ ኃይል ዘርፍ ልማት ለመደገፍ ተቋማቸው ስምምነት በመፈረሙ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ይህ ትብብር የፋይናንስ ክፍተቶችን ከመቀነሱም በላይ፤ በኢትዮጵያ የኢነርጂ መሠረተ-ልማት ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ይስባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቤኒን፣ ቡሩንዲ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ቶጎ፣ ኡጋንዳ እና ዛምቢያ ጋር በመቀላቀል ስምምነቱን የፈረመች 11ኛዋ አባል ሀገር ሆናለች ተብሏል፡፡

Exit mobile version